በ2017 የዋጁክ፣ ባላርዳንግ፣ ኪጃ እና ዩልፓሪትጃ ተወላጅ ክሊንተን ፕራየር፤ የነባር ዜጎች ማኅበረሰባት ውስጥ ያለውን ድህነት በመቃወም በመላ አውስትራሊያ በእግሩ ተጉዟል።
የ27 ዓመቱ ክሊንተን በአንድ ዓመት ከፐርዝ እስከ ካንብራ 6,000 ኪሎ ሜትሮችን በእግሩ አቋርጧል። በጉዞው ወቅት ከቪዲዮ ጋዜጠኛ አልፍሬድ ፔክ የፌስቡክ መልዕክት ደረሰው።
"ጉዞውን ለፍልሰተኛ ማኅበረሰባት ሰንዶ ለማጋራት እንደሚሻ፤ እንዲሁም፤ እራሱም መማርን እንደሚፈልግ።"
"እንደ ሰብዓዊ ፍጡር በእዚያ መንገድ፤ የሆነ ነገር እየሆነ እንደሁ ወይም አንድ ሰው የሆነ ነገር እያደረገ እንደሁ ልብ ያሰኛል። ግና እንደምን እነሱን መቅረብ እንደሚቻልና የመጀመሪያዋን እርምጃ ለመውሰድ ማወቅ ይሳን ይሆናል። እሱ ያደረገው ይህንኑ ነው" ሲል ክሊንተን ለSBS Examines ተናግሯል።
አልፍሬድ ከኢንዶኔዥያ ወደ አውስትራሊያ የፈለሰው ገና ታዳጊ ወጣት ሳለ ነው። የክሊንተን እግር ጉዞ ለእሱ "ወሳኝ ሁነት" እንደሆነ ገልጧል።
"እንደ አንድ ፍልሰተኛ፤ እኔም የአውስትራሊያን መሬት በመጋራት ተጠቃሚ መሆኔን አላውቅም ነበር። የአውስትራሊያ ዜጋ ስሆን፤ አውስትራሊያዊ መሆን ምን ማለት እንደሆነ ልብ በሚያሰኝ ረገድ አልተማርኩም። ከክሊንተን ፕራየር ጋር መሥራት እስከጀመርኩ ድረስ ተግዳሮቶችን በውል የተረዳሁ አልነበርኩም። ይህ ለእኔ ወሳኝ ሁነት ነበር" በማለት አስረድቷል።
ጓደኝነታቸው የተመሠረተው በ1966 የዕርቅ ሳምንት ንቅናቄ በተጀመረበት የዕርቀ ሰላም መንፈስ ነበር።
ሻንካር ካስይናታን፤ በብሔራዊ የዕርቅ፣ እውነትና ፍትሕ ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪ “እንደ እውነቱ ከሆነ፤ የዕርቅ ማዕከል አጋርነት ነው"ሲሉ ያመላክታሉ።
በማያያዝም "ኃላፊነትን ግድ የሚለው የእዚህ የአውስትራሊያ ታሪክ አካል ሆነናል . . . እንደምን ግንኙነቶችን ገንብተን ወደ ፊት ማምራት እንዳለብን አመላካች ነው” ብለዋል።
ከሽሪላንካ የእርስ በእርስ ጦርነት ሸሽተው የወጡት የታሚል ተወላጁ ሻንካር፤ ከመድብለባሕል ማኅበረሰባት ጋር የዕርቅ ጉዞዎቻቸውን አስመልክተው በመሥራት ላይ ይገኛሉ።
"አያሌ የፍልስተኛ እና ስደተኛ ማኅበረሰባት የሰው መሬት ወይም ንብረት ነጠቃ ምን ማለት እንደሁ በውል ይገነዘባሉ። በኃይል ተገድዶ መፈናቀልን፣ ባሕላዊ ድምሰሳን እንረዳለን።"
"ሆኖም፤ አዘውትረን ያን የእኛ የባሕር ማዶ ነዋሪ ወጎችና ታሪኮችን ከእኛ ነባር ዜጎች ጋር አናቆራኛቸውም። አንዴ ያ ግንኙነት ከተመሠረተ ዘላቂ ለሆነ ድጋፍና አጋርነት ብርቱ የሆነ መሠረት ይሆናል፤ የእውነተኛ ወዳጅነት አንኳርም ያ ነው ብዬ አስባለሁ” ብለዋል።
ይህ የSBS Examines ክፍለ ዝግጅት ብሔራዊ የዕርቅ ሳምንትን ይመለከታል፤ የፍልሰተኛ ማሕበረሰባት የአውስትራሊያ ዕርቅ ጉዞ ሚናን ይቃኛል።